የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት ለማሰራት የህንፃ ዲዛይንን አስመልክቶ ምክክር ተካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት (art school) ለመክፈት በዝግጅት ላይ ሲሆን ለትምህርት ቤቱ የሚሆን ህንፃ ለማሰራት የዲዛይን ምክክር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አካሂዷል፡፡

በዕለቱ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ ባህል የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ ባህልን ማወቅ እና ማሳወቅ አስፈላጊ ስለሆነ እና ዩኒቨርሲቲው በዚህ በኩል የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስኬድ የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት መከፈቱ አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ባይሌ በተጨማሪም አሁን የሚገነባው የኪነ ጥበብ ት/ቤት  ወደፊት ለባሕር ዳር እና አካባቢዋ በዘርፉ ትልቅ አስተዋፅ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ 
በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት የተገኙ ሲሆን ያሉንን ጥበቦች በተደራጀ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚደገፉበት እና የሚጠኑበት ብሎም በተግባር ለማሳየት የተቋማት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ይህንን የኪነ ጥበብ ት/ቤት ለመመስረት ያደረገውን መነሳሳት አድንቀዋል፡፡ ዶ/ር ሂሩት አክለውም የሚቋቋው ትምህርት ቤት በመጀመሪያ በእኛነታችን መመስረቻና መገለጫ ለሆነው ለአገራችን ባህላዊ ኪነጥበብ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ የኪነጥበብ ትምህርት ቤት ንድፍ በታሰበው መሰረት ተሰርቶ የምንጠብቀው ት/ቤት እውን እንዲሆን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከዩኒቨርሲቲው ጎን ሆኖ የቻለውንና የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚደያደርግ ተናግረዋል፡፡ 

በመክክር መድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡