የባሕር ዳር መሪ እቅድ / ማስተር ፕላን /

 

በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ላይ የማህበረሰብ የምክክር መድረክ ተካሄደ !!

በሙሉጌታ ዘለቀ                                                                                 

አንድን ከተማ ከተማ ከሚያደርገው አንዱና ዋናው  መሪ እቅድ / ማስተር ፕላን / ነው፡፡ የባህር ዳር ከተማም በከተማ አስተዳደሩና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሙሁራን የጋራ ትብብር የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን እቅድ ዝግጅት ላይ ከከተማዋ ማህበረሰ እና በከተማዋ ዙሪያ ከሚገኙ የሳተላይት ከተሞች ተወካዮች ጋር በባሕር ዳር የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡  

የአንድ ከተማ መሪ እቅድ ከ10 እስከ 30 ዓመታት የሚያገለግል ሆኖ የከተማዋን ቀጣይ እቀዶችና ንድፎች ለማስፈፀም የሚያገለግል ወሳኝ መሳሪያ ነው፡፡ መሪ እቅድ  /ማስተር ፕላን/ የከተሞችን እድገት በአግባቡ ለመቆጣጠርና የታለመላቸውን ጊዜ ሲያጠናቅቁ በሌላ መሪ እቅድ መተካት ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችው ባህር ዳር ከተማ እና በአራቱም መዓዘን የሚገኙት ሳተላይት ከተሞችን የጨመረ አዲስ መሪ እቅድ /ማስተር ፕላን/ ለመዘገጀት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀላፊነቱን ወስዶ በመስራት የዕቅዱን ከ60% በላይ አጠናቆ ቀሪዎችን የስያሜና ሌሎች ችግሮች ዙሪያ የክፍለ ከተሞች አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች እና ከሳተላይት ከተማዎች ተዎካዮች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ዳሬክተር የሆኑት ዶ/ር መንግስቴ አባተ ፕሮጀክቱ እስካሁን የመጣበትን የስራ እንቅስቃሴ እና በሂደቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉ አሀጉራዊ የተሸከርካሪ እና የባቡር መንገዶች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህንን ታሳቢ ያደረገ የአርባ አመት ማስተር ፕላን የከተማ አስተዳደሩ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ሙሁራን ጋር በመሆን እየተዘጋጀ መሆኑንና በእቅድ ደረጃ ጥናቶች እየተጠናቀቁ በመሆኑ በቀሪ የከተማዋ ችግሮች ላይ በመምከር ውጤታማ ስራን ለማከናዎን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር መንግስቴ ተናግረዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ተግዳሮት የሆነና የከተማዋን እይታ የሚያበላሹ  ህገወጥ የቤቶች ግንባታዎችን ህጋዊ ቅርፅ እንዲይዙ፣ የከተማዋን ነዋሪዎች  የቤት ፍላጎት እንዲፈታ እንዲሁም ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በዚህ ማስተር ፕላን ላይ የከተማዋ ህብረተሰብ ውይይት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ በሀይሉ መለሰ በውይይት መድረኩ ላይ የፕላን የችግር መተንተኛ ዛፍ ከስሩ እስከ ግንዱ /ስረ-መንስኤ፣ ቀጥተኛ መንስኤ እና አንኳር ችግሮችን/  በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ተሳታፊ የሆኑት የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ፍስሃ ፈንቴ እንዳሉት ባሕር ዳር ከተማ የሀገራችን ውብ ከተማ ከመባልም አልፋ ትልልቅ አለማቀፍ ጉባኤዎችን በብዛት ማስተናገዷ፣ በቱሪስት በብዛት የምትጎበኝ እና አላማቀፍ አውቅና ያላት በተፈጥሮዋ የታደለች ለምለም  ከተማ ነች ብለዋል፡፡ አዲሱ የከተማዋ ማስተር ፕላን ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ይዞላት እንደሚመጣ ተናግረው ለማስተር ፕላኑ እውን መሆን ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ ለተግባራዊነቱ ትብብር ሲጠየቁ ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ከተማዋን አረንጓዴ በማልበስና በተፈጥሮ ያገኘችውን የውሃ ሀብቶቿን በመጠቀም ነዋሪዎቿን የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ፕሮጀክቱ ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በመጨረሻም በፕሮጀክቱ ሂደት ዙሪያ ያጋጥማሉ ተብሎ በሚገመቱ እና አሁን ባሉ ችግሮች ዙሪያ ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከከተማዋ ነዋሪዎችና የስድስቱም ክፍለከተማ ተወካዮች እንዲሁም የሳተላይት ከተሞች ተወካዮች ጋር ከሃያ በላይ የከተማዋ ችግሮች ዙሪያ ምክክር ተደርጎ የጋራ መግባባት ተወስዷል፡፡