6ኛውን አለም አቀፍ ዓውደ ጥናት አካሄደ

ሂዩማኒቲስ ፋክልቲ 6ኛውን አለም አቀፍ ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋክልቲ በቋንቋ ፣ባህልና ተግባቦት ዘርፎች 6ኛውን አለም አቀፍ ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡
 
በአውደ ጥናቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲስ ፋክልቲ ዲን የሆኑት ዶ/ር ዳዊት አሞኘ አውደ ጥናቱ በቋንቋ መማር ማስተማር ፣ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት፣ በስነ-ፅሁፍ እንዲሁም በባህልና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ለተሳታፊዎችም አጠቃላይ ፋክልቲው የሚያስተምራቸውን የትምህርት አይነቶች እንዲሁም የሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ እያከናወነ ያለውን ተግባራትና ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አስረድተዋል፡፡
 
ዶ/ር ዳዊት አክለውም በዚህ አውደ ጥናት እንዳለፉት ሁሉ የካበተ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ምሁር ፕሮፌሰር ኬይ ሃይላንድ (Professor ken Hyland) ከውጭ አገር በማስመጣት እውቀታቸውን እና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተደርጓል፡፡
 
በአውደ ጥናቱ ፕ/ር ኪን ሀይላንድ ካቀረቡት ‹የአፃፃፍ ሚና ላይ ካተኮረው ፅሁፋቸው ባሻገር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ከሌሎች የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ የተለያዩ ምሁራን ከአስራ ዘጠኝ በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው በታዳሚው ውይይት ተደርጎባችዋል፡፡ ከቀረቡት ጥናታዊ ፁሁፎችም ከሶስት አራተኛ በላይ የሆነው ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ታውቋል፡፡
 
በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት እንደነዚህ አይነት አውደ ጥናቶች ከፍተኛ የልምድና የእውቀት ተሞክሮዎች የሚገኙባቸው መድረኮች ስለሆኑ ዩኒቨርስቲው ትኩረት ሰጥቶ ይሰራባቸዋል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋየ አክለውም ላገርም ሆነ ለዩኒቨርስቲው ገፅታ ግንባታ አጋዥ የሆኑትን የአየር መንገድ እና የግቢ ሹፊሮችን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተግባቦት ስልጠናዎች ቢሰጣቸው ጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡