ፕሮጀክቱ አመታዊ የገበሬ በዓል አከበረ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስር ያለው የተሻሻሉ የግብርና ምርቶችን ለማስፋፋት የአቅም ግንባታ በኢትዮጵያ /Capacity Building of Scaling up Production in Ethiopia (CASCAPE)/ የተሰኘው ፕሮጀክት በፋርጣ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ አመታዊ የገበሬ በዓል አከበረ

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ይኸነው ገ/ስላሴ የበዓሉ ዋና አላማ ፕሮጀክቱ በተለያዩ አርሶ አደር ማሳዎች ላይ ያከናወናቸውን ተግባር ተኮር ስራዎች (ለሙከራ የተዘሩትን) በመጎብኘትና በማስተዋወቅ ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከመጡት ባለድርሻ አካላት ጋር ከምልከታው በተገኘው ግብዓት ላይ ውይይት ተካሂዶ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ ለመለየት ታልሞ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ የምርምር ባለሙያ አቶ የኔሰው አበበ የበዓሉን መርሐ-ግብረ ሲያስተዋውቁ ተሳታፊዎች ከአካባቢው አርሶ አደሮችና የልማት ጣቢያ ተጠሪዎች ጋር ከአብክመ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የግብርና እድገት ፕሮግራም፣ የእንስሳት ጽ/ቤት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከዘር ብዜት ተቋማትና ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ሲሆን ፕሮጀክቱ ያከናወናቸውን ተግባሮች ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት በዓሉ ለአርሶ አሩም ሆነ ለባለሙያው የማንቂያ ደወል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከመስክ ጉብኝቱ በተጨማሪ በታዩት ነገሮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ አርሶ አደሮች መሟላት የሚገባቸውን ነገሮች እንዲሟሉ ጥያቄ አቅርበው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መልስ ሰጥተውበታል። የአብክመ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ሊቃውንት ይኸይስ በአካባቢው ማህበረሰብ የተለመደው የግብጦ ዝርያ ለሰውም ሆነ ለከብት መኖነት አስቸጋሪና ለመመገብ የሚያዳግት የነበረ ሲሆን በምርምር ስራቸው ያገኙትና ከጀርመን ሀገር ያመጡት የግብጦ ዝርያ ግን ከነባሩ በእጅጉ የሚለይና የፕሮቲን መጠኑም ሆነ ጣፋችነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው ለበግ ማድለቢያም ሆነ ለወተት ላይ መኖነት ከፋጉሎና ከፉርሽካ የበለጠ ግብዓት የሚሰጥ ስለሆነ በተለያዩ አርሶ አደር ማሳ ላይ በመጠኑ ተዘርተው የታዩትን በማስፋትና በእንስሳት እርባታ ስራ በመሰማራት ወደ ጥሩ የአኗኗር ደረጃ ለመድረስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም አዲስ የተገኘው ጣፋጭ ግብጦ በሚዘራበት ወቅት መጠነኛ የመሬት እርጥበት ብቻ እንደሚበቃውና ውሀ በሚያቆር ቦታ ላይ ፈጽሞ መዘራት እንደሌለበት ተናግረው ውሀ ማንጣፈፍ በሚችል ማሳ ላይ ከተዘራ ግን ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝና ለመሬት ለምነትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ለታዳሚው ገለጻ አድርገዋል።

አርሶ አደሮችም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከአሁን በፊትም የተለያዩ የቢራ ገብስ፣ድንችና ሌሎች የሰብል ዝርያዎችን በማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ከታላቅ ምስጋና ጋር ገልፀው የአካባቢው መሬት ለም ባለመሆኑ ምክንያት አጥጋቢ ምርት ለማግኘት ስለማይቻል ፕሮጀክቱ ያመጣውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማሳቸውን ከምርምር የተገኙትን የከብት መኖ ዝርያዎች በመዝራት በእንስሳት እርባታ ስራ ላይ ለመሰማራት ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል፡፡