የአደገኛ-እፅ ተጠቃሚነት

                      በአደገኛ-ፅ ተጠቃሚነት ዙሪያ የምክክር አውደ ጥናት ተካሄደ

በወንዳለ ድረስ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከመቋሚያ የማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር መስከረም 20 በሴኔት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዩኒቨርሲቲን መሠረት ያደረገ የፀረ ሱስ ንቅናቄ ለማድረግ የአንድ ቀን አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ አዲስ ተማሪዎች በአንዳንድ በሱስ ተጠቂ ጓደኞቻቸው ምክንያት ወደ ሱስ የመግባት ችግር እንዳለ አውስተዋል ፡፡ ለዚህም ዶ/ር ተስፋዬ  እንዳሉት መምህራን፣ ሰራተኞችና ኃላፊዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው የአካባቢው ማህበረሰብም ተማሪዎችን ሱስ የሚያሲዙ የንግድ ቦታዎችን ከመክፈት ቢቆጠቡ በሚል የምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ከአውደ ጥናቱም ጠንከር ያለ ተቋም የመፍጠርና ቀጣይነቱ ላይ መስራት ይጠበቃል ብለዋል ፡፡

በአውደ ጥናቱ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት የመቋሚያ ማህበረሰብ ልማት ማህበር መስራች እና ዋና ስራ አስኪሃጅ  አቶ ኤልያስ አላዩ ማህበሩ በሀረማያ፣ ሀዋሳና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች የፀረ ሱስ ንቅናቄ በማድረግ እስካሁን ከ600 በላይ ወጣቶችን ከሱስ መታደግ የቻለ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በመንቀሳቀስ ከአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነትና  ሱሰኝነት ራሱን መጠበቅ የሚያስችል ቁመና ያለው ህብረተሰብ መፍጠር የመህበሩ አላማ መሆኑን ጠቁመው የአደገኛ-እፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ዘር ፣ ቀለም ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣  ስራ፣ እድሜና የኑሮ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያጠቃ ተናግረዋል፡፡ በጣም አስከፊ የሆነው የአደገኛ-እፅ ጥፋት፤ አምራች የሆነውን የኢኮኖሚ ክፍል ማለትም ወጣቱን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨረሰ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ የሃይማኖት ተቋማትና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን ጨምሮ በከተማው የሚገኙ ተቋማት በመገኘት የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በሱስ የመጠመድ ሂደት ላይ ትኩረት ሰጥተው የተወያዩ ሲሆን በቀጣይም ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት ኮሚቴ በማቋቋም ጠንከር ያለ ስራ ለመስራት እቅድ ይዘዋል ፡፡