የመፅሐፍ ምረቃ

                                  የመፅሐፍ ምረቃና ግምገማ ተካሄደ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም አማካኝነት በዩቨርሲቲው የሲቨል ምህንድስና መምህር በሆኑት እንዳላማው አራጌ ተደርሶ ለንባብ የበቃው ‹‹ግንጥል ልዕልና በኢትዮጵያ››  በተሰኘው መፅሐፍ ዙሪያ ሙያዊ ሂስ እንዲሰጥበት የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዷል፡፡

በመፅሀፉ ዙሪያ የተለያዩ ፅሁፎች በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ቀርቧል፡፡ ሙሁራኑ  ‹‹ግንጥል ልዕልና በኢትዮጵያ›› የተሰኘውን መጽሃፍ በተለያየ መነጽር ያነበቡት ሲሆን ከኢትዮጵያ ታሪክ አንፃር ዶ/ር ዋጋው ተሾመ ፣ ከማንነት እና ከህብረት ሚስጥር አንፃር አቶ ጴጥሮስ ክበበው ፣ ከመንፈሳዊ እይታና ስነ አስተምሮ አንፃር ደግሞ ዶ/ር መስከረም ለቺሳ በመጽሀፉ ላይ ያላቸውን ምልከታ ለውይይት በሚመች መንገድ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች መፅሐፉ በያዛቸው በርካታ ንዑስ ርዕሶች ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተው ፤ በመፅሀፉ ደራሲ እንዳላማው አራጌ ምላሽ ተሰጦባቸዋል፡፡ በውይይቱም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ፕሬዘዳንት የሆኑት ሊቀ ህሩያን በላይ መኰነን ስነ-ጽሐፍ እና ስነ-ሂስ አብረው የሚሄዱና ሊዳብሩ የሚገባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በየጊዜው ለንባብ የሚነቁት መጽሀፍት ደረጃቸው ከፍ ሊል የሚችለውም በየጊዜው ሲተቹና ሲገመገሙ መሆኑን ተናግረው ሂስን የምንፈራ ከሆነ ስነ ፅሁፍ ወደኋላ እንጅ ወደፊት የሚራመድበት እድሉ የጠበበ መሆኑን በአንክሮ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም በዩኒቨርስቲው አመራርና መምህራን እንዲሁም በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ፕሬዘዳንት በሆኑት ሊቀ ህሩያን በላይ መኰነን አማካኝነት  መፅሐፉ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ለንባብ  ክፍት ሆኗል፡፡

 

Date: 
Friday 25, 2019
place: 
Bahir Dar University
February, 2019