ማህበሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ-ጥናት አካሄደ

የኢኮ-ቱሪዝም እና ብዝሃ-ህይወት ጥበቃ ማህበር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቤዛዊት ቤተ መንግስት የወፍ ቆሎ (ሣንታና ካማራ) የተሰኘውን መጤ አረም ማስወገድና መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ለማስጀመር የግማሽ ቀን አውደ-ጥናት በቤንማስ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡
ማህበሩ የኢትዮጵያ በጐ አድራጐት ማህበር ሆኖ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለማህበሩ በሰጠው 25 ሄክታር የሚሊኒየም ፓርክ ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የወፍ ቆሎ (ሣንታና ካማራ) የተሰኘውን መጤ አረም  ለማስወገድና መልሶ ለማልማት አውደ-ጥናቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ከእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ጋር ያስተላለፉት የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አያሌው ወንዴ  ናቸው፡፡
የፕሮግራሙን የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ ጥሪውን አክብረው ለመጡት ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውንና ፕሮግራሙን ላዘጋጀው አካል ምስጋና አቅርበው ዩኒቨርሲቲው ከአሁን በፊት የተለያዩ መጤ አረሞችን በማጥፋት ዘመቻ በስፋት ሲሳተፍ እንደቆየ ገልፀው የወፍ ቆሎን (ሣንታና ካማራ) የተሰኘውን መጤ አረም ለማጥፋትና በሌላ አገር በቀል ዛፎች በማልማት ፓርኩ የምርምር ማዕከልና የሚጐበኝ ማራኪ ቦታ ይሆን ዘንድ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡ ም/ፕሬዚዳንቷ አያይዘውም በፅንሰ ሀሳብ የቀረበው ወደ ተግባር እንዲቀየርና ፓርኩን የማልማት ሥራው እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሙህራንና የማህበሩ አባላት ሲሆኑ 80% የሚሆኑ አባላት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች እንደሆኑ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለማህበሩ መመስረትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከገንዘብ ድጋፍ ጀምሮ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዝታ የኔአለም ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ለወደፊት ፖርኩ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መስፋፋትና መጠናከር እንዳለበት ከቤቱ ተጠቁሞ የቀረቡት ፅሁፎች የመነሻ ሀሳብ እንደሆኑና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የቤት ሥራ አድርጐ እንዲወስደው ብሎም በእኔ ባይነት ስሜት ማህበሩ እንዲስፋፋ ከታዳሚዎች ሀሳብ ተሰንዝራል፡፡