አቋማተ ስልጠና ሰጠ

የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም (አቋማተ) በዋግህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ላቋቋመው ለአማርኛ ቋንቋ መምህራን ክበብ አባላት የ2 ቀን ስልጠና ሰጠ፡፡
ስልጠናው ሥነጽሑፍን ለአማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያነት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ የአማርኛ ቋንቋ አብይና ንዑሳን ክሂሎችን ምን ምን እንደሆኑ፣ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የማስተማሪያ ሥነዘዴዎችን፣ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት አመታዊ፣ ዕለታዊና የምዕራፍ እቅዶች አዘገጃጀት እና የተለያዩ የስነልሳናዊ እሳቤዎችን በተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ የቀረበ ነበር፡፡

ስልጠናውን የተከታተሉት የአማርኛ ቋንቋ መምህራን በቀረበላቸው የስልጠና ይዘቶች ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፤ ግልፅ እንዲሆንላቸው በፈለጉት ርዕሶች ላይም ጥያቄዎችን አንስተው በአሰልጣኙ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ቋንቋ መምህርና የሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ ም/ዲን የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ይታየው በርዕሶቹ ላይ ያዘጋጁትን ስልጠና ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡
በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ላይ የሚታየውን የሥነልሳን እውቀት ክፍተት ለመሙላት ይቻል ዘንድ የስነልሳን ስልጠና በሰፊው እንዲሰጣቸው ሰልጣኞች ሀሳብ አቅርበዋል።

ሰልጣኞች አክለውም አቋማተ በሌሎች ከተሞች ከሚገኙ የአማርኛ ቋንቋ መምህራን ክበባት ጋር በጋራ የሚወያዩበት የልምድ ልውውጥ መድረክ እንዲያመቻች ጠይቀዋል።
መምህራኑ ያነሱትን ጥያቄ በመመለስ ለቀጣይ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የልምድ ልውውጥ መድረኮችን እንደሚያመቻችና የአማርኛ ቋንቋ መምህራን ክበብ ጥምረት በቅርቡ እንደሚመሰረት የአቋማተ ዳይሬክተር ዶ/ር ኂሩት ካሳው ገልጸዋል።
በስልጠናው ከ1ኛ ክፍል እስከ መሰናዶ ትምህርት ደረጃ የሚያስተምሩ 55 የአማርኛ ቋንቋ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

በስልጠናው ከአማርኛ ቋንቋ መምህራን በተጨማሪ 28 የኸምጣጛ ቋንቋ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን የኸምጣጛ ቋንቋን ለማስተማር የሚያግዝ እውቀት እንደጨበጡ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኸምጣጛ ቋንቋን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሰራ መሆኑንና በተለይም በሥርዓተ ጽሕፈቱ ላይ ምርምር ለማካሄድ የተመራማሪዎች ቡድን የተቋቋመ መሆኑን ዶ/ር ኂሩት ካሳው ገልጸዋል።

Share