መግቢያ

አማርኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነገሩት የደቡባዊ ሴም ቋንቋዎች አንዱ ሲሆን ቀደም ሲል የሥራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ግዕዝ በመተካት 10ኛውና 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መካከል ባለውጊዜ የስራ ቋንቋሆኖ ማገልገል እንደጀመረ ባየ (1987) እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ማዕከል(1993) ይገልፃሉ። በኋላም 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሥነ ጽሑፍ ጭምር እያደገ መጥቶ በተለይ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ የተሻለ እድገት በማሳየት አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል። 

የአማርኛ ቋንቋ ለረዥምዓመታትየስራናየትምህርትቋንቋሆኖእንዳገለገለምታወቃል (ተሾመ፣1979)የሚሲዮናውያንንወደ ኢትዮጵያመግባትተከትሎየመስበኪያናየመጽሐፍቅዱስማስተማሪያቋንቋከመሆኑምበላይ1951 .. ጀምሮ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የማስተማሪያ ቋንቋሆኖእስከ ደርግመንግስትፍፃሜድረስ አገልግሏል። ቋንቋው ለማስተማሪያ ቋንቋነት የተመረጠው ደግሞ ከመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ይወጡ የነበሩ መምህራን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለማስተማር የነበራቸው ዝግጁነት የሚጠበቀውን ያህል ብቁ ባለመሆኑ ነው (ሀብተማርያምናሌሎች፣ 1979) 

የአማርኛቋንቋ በአፄ ኃይለ ላሴ ዘመነ መንግስት ብሔራዊ ቋንቋ የነበረ ሲሆን፣ በደርግና በኢፌድሪ መንግስታት ደግሞ በስራ ቋንቋነት፣ አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛልበአሁኑጊዜበኢትዮጵያውስጥከሚኖረውህዝብ (29.42%) በአፍመፍቻቋንቋነት ሲናገረው በርካታቁጥርህዝብደግሞበሁለተኛቋንቋነትለምዶታል (ማዕከላዊስታትስቲክባለስልጣን፣ 2008) 

ቋንቋው አሁንም ባለው ሰፊ ስርጭት አማካኝነት አገራዊና ክልላዊ ሚና እንዲጫወት ህገመንግስታዊ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት የስራ ቋንቋ እንዲሆንና በአገር ደረጃ ለሚደረጉ ግንኙነቶች መግባቢያ ሆኖ እንዲያገለግል ሃላፊነት የተሰጠው ሲሆን ተግባሩንም እንዲወጣ በሁለተኛ ቋንቋነት ለሁሉም ክልል በትምህርትነት ከ3ኛ/ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአማራ ክልል የስራና የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቋንቋ እንዲሆን የተሰጠውን ሃላፊነት ከመወጣቱ ባሻገር ቋንቋው ለኢትዮጵያዊያን ቅርብ ከመሆኑ የተነሳም ሌሎች ክልሎችም የስራና የትምህርት ቋንቋ አድርገው እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡ 

ሆኖም ግን አማርኛ ቋንቋን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲና በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉ የተለያዩ አውደ ጥናቶችና ውይይቶች፣ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ መገናኛዎች በቋንቋው አጠቃቀም ዙሪያ ጉልህ ችግሮች እየታዩና ይህም ችግር በቋንቋው የመደበኛነት ደረጃ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ይገለጻል፡፡  የቋንቋ ትምህርቱም ቢሆን የሚታየውን ችግር መቅረፍና ተፈላጊውን የቋንቋ ችሎታ በተማሪዎች ዘንድ ማስገኘት እንዳልቻለም ይነገራል፡፡ ይህንም አስመልክቶ ፕሮፌሰር ሽፈራው (2005፣1) በዩኒቨርሲቲያችን በተደረገ አገር አቀፍ አውደ ጥናት ላይ ‹‹የቋንቋው ጥራት እየደከመ፣እንዲያውም እያሽቆለቆለ መጥቷል የሚል ሂስና ሀዘን ከፍ ባለ ድምፅ ባደባባይ ሲገለፅ መስማት እየተለመደ መጥቷል›› በማለት ማህበረሰቡ የሚሰጠውን አስተያየት ገልፀዋል፡፡ ባንፃሩም ቋንቋው ሳይንስና ቴክኖሎጂን የመግለጽ ብቃቱን በማሳደግ ለሰፊ አገልግሎት (የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት መማሪያና ማስተማሪያ ቋንቋ) እንዲውል ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡ በአጠቃላይ ችግሩን በመቅረፍ የቋንቋውን መደበኛነት በማሳደግና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትና ለዚህም ሃላፊነቱን የሚወሰድ ተቋም መኖር እንዳለበት በተለያየ ጊዜ ይገለጻል፡፡ 

የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋምን በተመለከተ የነበረው ልምድ እንደሚያመለክተው ጣሊያን ከኢትዮጵያ በጦርነት ተሸንፎ ከወጣ ከአንድ አመት በኋላ የአማርኛ ቋንቋን ሰዋስዋዊ ስርዓት የሚገልጽና በቋንቋው ላይ የሚሰራ ተቋም በማስፈለጉ ተቋሙ በትምህርትና ስነጥበብ ሚኒስቴር ሃላፊነት ስር ተቋቁሞ እንደነበር ፍልማን (1978) ያስረዳሉ፡፡ በ1968 ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተቋም ተቋቁሞ እንደነበርና ይህም በትምህርትና በስነጥበብ ሚኒስቴር ይመራ እንደነበር፤  ሳይውል ሳድርም በ1972  ‹‹የአማርኛ ቋንቋ ጥናትና ምርምር ተቋም›› ተብሎ እንደተለወጠ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል ተቋም በድረ-ገጹ አስፍሯል፡፡ ይህም ብዙም ሳይቆይ በ1975 ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተቋም›› ተብሎ እንደገና እንደተሰየመና በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስር እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ይህ  ተቋም በ1981  ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ‹‹የአማርኛ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቃላት ትርጉም ፕሮጀክት›› የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የስነህይወት፣ የሂሳብ፣ የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪ፣ ወዘተ. ቃላትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ እንዲተረጎም አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ የጊዜና የልምድ ማነስን የነበረበት ቢሆንም፣ አማርኛ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የመግለጽ አቅም እንዳለው ብርሃን የፈነጠቀና መሰረት የጣለ ፕሮጀክት ነው (ኤርሚያስና ደምሱ፣2013)፡፡  በኋላም በ1997 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛውሮ ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የምርምር ተቋም›› ተብሎ ተመስርቷል፡፡ በመጨረሻም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከባህል ሚኒስቴርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመመካከር በ2010 ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል ምርምር ተቋም›› ተብሎ እንዲያድግና እንዲሰየም በማድረግ አገራዊ ሃላፊነቱን ወስዷል (አማንዳና ራሄል፣2011)፡፡ ይህ ተቋም ዋና ሃላፊነቱ የኢትዮጵያን ቋንቋዎችና ባህሎች  ማጥናት፣ መሰነድ፣ መጠበቅ እና ማስተዋወቅ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን ማሰራጨት፣ በስርዓተ ፅህፈትና በሰዋሰው ላይ ምርምር ማድረግ፣ ስነቃሎችን፣ አገር በቀል እውቀቶችን መሰብሰብና መሰነድ፣ መዝገበቃላትን ማሰባሰብ፣ ማዘጋጀት፣ ማሳተም እና በተለያዩ ቋንቋዎች የመማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍትን ማዘጋጀትን ሁሉ ያካትታል፡፡

እንግዲህ ቀደም ብሎ ለማሳየት እንደተሞከረው የአማርኛ ቋንቋ ጥናትና ምርምር ተቋም በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ እንደነበርና ወዲው ግን ኢትዮጵያ የብዝሀ ቋንቋ አገር በመሆኗ ወደኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተቋም እንደተለወጠ ተመልክተናል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር ቋንቋዎችን የሚያጠና፣ የሚጠብቅ የሚያስተዋውቅ፣ የሚሰንድ፣ ወጥ አጠቃቀም እንዲኖር የሚያስተምርና በዚህም ቋንቋውን ወደ መደበኛነት በማሳደግ ለሰፊ አገልግሎት እንዲውል ማድረግ የሚችል ስርዓትና የቋንቋ ተቋም አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡  አማርኛ ቋንቋ በአገራችን ካለው ሰፊ አገልግሎት አኳያ አሁን ያለበትን ሁኔታ ስንመለከት ከእንግሊዝኛና መደበኛ ካልሆኑ ቃላት ጋር በማቀላቀል ወጥ ያልሆነ አጠቃቀም የሚታይ ከመሆኑም በላይ የቋንቋው የመደበኛነት ደረጃ ዝቅ እንዲልና አሁን ባለውም ሆነ ወደፊት ሊኖረው በሚችለው ሰፊ አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ ሊደርስበት እንደሚችል  የሚጠቁም ነው፡፡

ሌላው አማርኛ በአፍ መፍቻ ቋንቋነትም ሆነ በሁለተኛ ቋንቋነት በኢትዮጵያ ሰፊ ስርጭት ያለው ቋንቋ ከመሆኑም በላይ ከኢትዮጵያ ውጭም በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በእስራዔል፣ በግብጽ፣ በሲዊድንና በአሜሪካ ተናጋሪ እንዳለውና በአሜሪካ በዋሽግተን የስራ ቋንቋ እንደሆነም ይታወቃል (አማንዳና ራሄል፣2011)፡፡ ቋንቋው በአገር አቀፍ ደረጃም ለመግባቢያነት እያገለገለ ሲሆን ሰፊ የሆነ የስነጽሁፍ ሀብትም አለው፡፡ ይህ ቋንቋ በሁለተኛ ደረጃና በከፍተኛ ትምህርት ተቋም በአማራጭነትም እንኳ የመማሪያና የማስተማሪያ ቋንቋ መሆን አልቻለም፡፡ ለዚህም በአብዛኛው የሚቀርበው ምክንያት ሳይንስና ቴክኖሎጂን በበቂ ሁኔታ መግለጽ አይችልም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ቋንቋው ሳይንስና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መግለጽ እንዳይችል ያደረግነው እኛ በቋንቋው ላይ ስላልሰራን እንጅ ቋንቋው አቅም  እንዳለውና አሁንም ሳይንስና ቴክኖሎጂን መግለጽ የሚችል ቋንቋ እንደሆነ ፕሮፌሰር ሽፈራው (2005) የዘመናዊ ወታደራዊ ውጊያ፣ የፍታብሄር፣ የወንጀል፣ የንግድ ቋንቋ እንደሆነና በከፍተኛ ትምህርት የባህል ጥናት (የፎክሎር) እና የተግባራዊ ስነልሳን ሳይንሶችን እስከ 3ኛ ዲግሪ ትምህርት ድረስ ለመማሪያና ለፍልስፍና ደረጃ እንደበቃና ቋንቋው ብቃቱ እንዳለው በማሳያነት በመግለጽ ለከፍተኛ ትምህርት መስጫነት እንዲውል ታስቦ ብዙ ርቀት እንደተሄደም ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን የቋንቋው እድገት ፍጥነቱ እንደቀነሰና ለዚህም ብዙ ነገሮች በምክንያትነት ሲጠቀሱ እንደሚስተዋልና በዚህ ላይ ሃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራ የተደራጀና ጠንካራ ተቋም ሊኖር እንደሚገባና ለዚህም በማስተማሩና በምርምሩ ተግባር የተሰማሩ ዩኒቨርሲቲዎች ትልቁን ሚና ሊወስዱ ይገባል፡፡ ሌሎች አገሮች ቋንቋቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ እንዲሆን ያደረጉት ከውጭ ወደአገራቸው የሚገባውን ፅንሰሃሳብና ቃላት ዝም ብለው በመቀበል ሳይሆን ለስነልሳንና ለቋንቋ ባለሙያዎቻቸው ለአዳዲስ ጽንሰ ሃሳቦችና የውጭ ቃላት በራሳቸው ቋንቋ ስያሜ እንዲሰጡና ለቋንቋው ተናጋሪ የተለያዩ መገናኛዎችን በመጠቀም እንዲያሳውቁ የማድረግ፣ እንዲሁም የቃላት ባንክ በማቋቋም ቃላትን መፍጠርና መሰነድ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንዲሆን ሃላፊነቱን በመስጠት ነው፡፡    

በመሆኑም ከላይ ከቀረቡት ሃሳቦች በመነሳት በአማርኛ ቋንቋ ላይ የሚታዩትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ፣ የቋንቋውን አጠቃቀምና የመደበኛነት ደረጃ ለማሻሻልና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ በማድረግ ለሁለተኛ ደረጃና ለከፍተኛ ትምህርት የማስተማሪያ ቋንቋ ብቁ እንዲሆን ለማድረግ  ስርዓት መዘርጋትና ለዚህም ሃላፊነቱን ሊወስድ የሚችል ተቋም መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ‹‹የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋምን›› መመስረት አስፈላጊ ሆኗል፡፡

እንደሚታወቀው አማርኛ ለኢትዮጵያ ህዝብ አገራዊ/ፌደራላዊ የመግባቢያ ቋንቋ በመሆን ያገለግላል፡፡ ቋንቋው በአብዛኛው የአማራ ክልል ህዝብ ደግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠን ህዝቡን ከማግባባቱ በላይም የመማሪያ፣ የስራ፣ የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ በመሆን ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ማንኛውም ክልል የራሱን ባህልና ቋንቋ የማሳደግና የማበልፀግ ሃላፊነትና መብት እንዳለውም በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ይህንም በተመለከተ ሌሎች ክልሎች ለምሳሌ ደቡብ ህዝቦችን በአብነት ብንወስድ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ተቋማትን መስርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ተግባራቸውም ለሌሎች በአርአያነት ሊወሰድ ይገበዋል፡፡ በአማራ ክልልም ባህልንና ቋንቋን በማሳደግ ረገድ ባህልና ቱሪዝም እየሰራ ያለው ስራ ከፍተኛ የሆነ ውጤት ያስገኘ ቢሆንም አማርኛ ቋንቋን በተመለከተ ግን አሁን እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍና የቋንቋውን መድብለ ቃላት በማሳደግ የመደበኛነት ደረጃውን በማስጠበቅና ለሰፊ አገልግሎት እንዲበቃ ለማድረግ የሚሰራ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው ተቋም የለም፡፡ ይህን ሃላፊነት ሊወስድ የሚችል ተቋም ሊመሰረት የሚገባው ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ቋንቋውን ለማሳደግ የሚሰሩ ስራዎች በአብዛኛው የስነልሳንና የቋንቋ ባለሙያዎችን የሚጠይቅ ሙያዊ ተግባር በመሆኑ ነው፡፡

በመሆኑም ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በመገኘቱ፤ በቋንቋ የሚታዩትን ችግሮች በመቅረፍ የበኩሉን የመወጣት ማህበረሰባዊና ሙያዊ ሃላፊነቱን መወጣት ስለሚገባው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ያሉት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራን ከምርምር ባሻገር ችግሩን  ተግባራዊ ስራዎችን በመስራት መቅረፍ የሚያስችል ሃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያስችል እውቅና፣ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው ተቋም ስለሚያስፈልጋቸው የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም በዩኒቨርሲቲያችን ማቋቋም አስፈልጓል፡፡

Share